❖የእመቤታችን የእራት ግብዣ ድንቅ ምስጢር በቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ❖
በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
✔❖ አንድ ድንቅ የኾነ ምክር እናገረው ዘንድ አነሣሥቶኛልና፣ አንተ የምታስተውል የነፍስኽን ጆሮ ወደ ርሱ አዘንብል! ራሱን በድንቅ ይገልጥ ዘንድ የእመቤታችን የማርያም ዝና በውስጤ እየተላወሰ ነውና፣ በማስተዋል አእምሮህን አዘጋጀው! ስለ ርሷ እናገር ዘንድ ቅድስት ድንግል ጠርታኛለችና፣ ነገርዋን እንዳናቀልለው ለአንጸባራቂው ዝክርዋ ጆሯችንን እናጥራ፡፡ የሰማዩ ጌታ በማሕፀኗ ያደረው ኹለተኛዪቱ ሰማይ፣ በጨለማ ላሉትም ያበራ ዘንድ ብርሃን ኾኖ ከርሷ ወጣ፡፡ ከሴቶች ኹሉ የተባረከች የኾነችው የምድሪቱን መርገም ለማንሣት ምክንያት ኾነች ኩነኔም (ፍርድም) ከእንግዲኽ ወዲያ አይኖርም፡፡
✔❖ትሕትና ብጽዕት በቅድስና ደም ግባትም የተመላች ስለኾነችው፣ ስለርሷ አንዳች ቃል ስንኳ ለመናገር አፌ ብቁ አይደለም፡፡ የዚኽችን ብጽዕት ገጽታ መሳል እንዴት ኾኖ ይቻለኛል፣ እኔ የምቀምመው ቀለም ተራ እና ለርሷ የማይመጥን አይደለምን? የርሷ ውብ መልክ እኔ ከምቀኘው ቅኔ እጅግ የላቀና የከበረ ነው፤ ውበቷን (ገጽታዋን) ይስል (ይገልጽ) ዘንድ አእምሮዬም አይሞክረውም፡፡
✔❖ የእመቤታችን የማርያምን ታሪክ (ዝና) በምላቱ ከመንገር ይልቅ፣ ፀሓይን ከነብርሃኗና ከነሙቀቷ መግለጽ ይቀላል፡፡ ምናልባት የጠፈርን ብርሃናት በሰማይ ላይ መያዝ ይቻል ይኾናል፣ የእርሷ ዜና ግን በሰባክያን ኹሉ እንኳ ቢነገር በፍጹም አያልቅም፡፡ ማንም ልሞክር ቢል እንኳ፣ በምን ምድብ ይገልጻታል (ይመድባታል)? ምንኛስ ቢጠበብና ቢቀኝ ሊናገር ይችላልን? ከደናግል (ይመድባታል)፣ ወይስ ከጻድቃን፣ ወይንስ ከብፁዓን? ካገቡት ሴቶች (ከመዐስባት) ይኾን፣ ወይስ ከእናቶች፣ ነው ወይስ ከአገልጋዮች? እነሆ የክብርቲቱ አካል የድንግልናን እና የወተትን ምልክት (ምስክርነት) ተሸክሟል፣ ፍጹም ወሊድ፣ ነገር ግን የተዘጋ (የታተመ) ማሕፀን፤ ከርሷ የሚስተካከል (አቻ የሚኾን) ማነው?
✔❖ ካለገቡ ደናግል ጋር ያለች ሲመስል፣ እንደ አገልጋይ ኾና ለብላቴናው ክርስቶስ ወተት ስትሰጥ አያታለኊ፡፡ እጮኛዋ (ጠባቂዋ) ዮሴፍ አብሯት እንደሚኖር ስሰማ፣ የምመለከታት ርሷ ግን በጋብቻ ሥርዓት ከወንድ ጋር አንድ አልኾነችም፡፡ ከደናግል ተርታ (መኻከል) ትኾን ብዬ ስፈልጋት፣ የመውለዷ ነገር ከዦሮዬ ይገባል፡፡ ከዮሴፍ የተነሣ የታጨች ሴት ትኾን ብዬ አስባለኊ፣ ግን ደግሞ አንድ ስንኳ ፍጡር (ተባዕት) ያላወቃት መኾኗን አምናለኊ፡፡
✔❖ እንደ ማንኛዋም ወላድ እናት ወንድ ልጅን የወለደች መኾኗን አይቻለኊ፣ ግን ደግሞ ከደናግል ተርታ እንደኾነች ይታየኛል፡፡ እርሷ ድንግልም፣ እናትም፣ የአንድ ሰው (የዮሴፍ) እጮኛ ኾና ግን ወንድ ፈጽሞ ያላወቃት ናት፣ እናም ሊገነዘቧት የማትቻል መኾኗን እየተረኩ (በተቃራኒው) ስለርሷ መናገር እንዴት እችላለኊ?
✔❖ ስለ ርሷ ለመናገር ፍቅር አስገድዶኛል፣ ይኽም ተገቢ ነው፣ ነገር ግን የዝናዋ (የትረካዋ) ከፍታ ለኔ እጅግ ከባድ ነው፤ ምን ላደርግ እችላለኊ? የበቃኊ ኾኜ እንደ ማላውቅ አኹንም እንዳልሆንኹ በግልጽ አውጃለኊ፣ ግን ያስገደደኝ ፍቅር ስለኾነ ከኹሉ በላይ ከፍ ያለውን ዜና አኹንም እተርካለኊ፡፡ ፍቅር ዘለፋን አይናገርም፣ ለሚሰማውም ደስታና ብልጽግና ያጐናጽፋል፡፡ በመገረም ቆሜ እየተደነቅኊ ስለ እመቤታችን ማርያም እናገራለኊ፣ ምክንያቱም የምድራዊ ፍጡራን ዘር (ሴት ልጅ) የኾነችው ርሷ ወደ ታላቅ ማዕርግ ከፍ ብላለችና፡፡
✔❖ ጸጋ ራሱ ወልድን በርሷ ይልክ ዘንድ በማዘንበሉ ነው፣ ወይንስ ርሷ የአምላክ ልጅ እናት ለመኾን ያበቃት ውበት ስለነበራት ነው? እግዚአብሔር ወደ ምድር መውረዱ በጸጋው (በቸርነቱ፣በፈቃዱ) እንደኾነ ግልጽ ነው፣ እመቤታችን ማርያምም ንጽሕት ስለነበረች ርሱን ተቀበለችው፡፡ እርሱ ትሕትናዋን፣ ደግነቷን እና ንጽሕናዋን ተመለከተ፣ ከትሑታን ጋር ማደር ስለሚቀልለውም ርሱ በርሷ (ውስጥ) ዐደረ፡፡ “ወደ ትሑቱና ዝቅ ወዳለው ካልኾነ በቀር ወደ ማን አመለከታለኊ?” ሲል ርሷ ከትውልድ መኻከል ትሕት ስለነበረች ርሱ ተመለከታት በርሷም ዐደረ፡፡
✔❖ እናቱ ልትሆን የወሰዳትን ድንግል እርሱ አላጎደፋትም፡፡ በቃላቶቼ የሚቆጣውን፣ እና የተጣመመውንና ግራ የተጋባውን እኔ የምናገረውን ንግግርም ለመስማት የማይሻውን ሞኝ (ከቶ ምን ላድርገው)? ጆሮው ለደነቆረ የነጐድጓድ ድምጽም ታላቅ ፀጥታ ነው፣ ፍጥረት ሁሉ ቢዘምር ደግሞ እሱ አይሰማም፡፡ ዐሥር ሺሕ ፀሐዮች ቢወጡ እንኩ የዕውሩ ዓይን ጨለማን ስለተለማመደ ቀኑ ለሱ አይጠቅመውም፡፡ በነውርና በመከፋፈል እብሪት ለተመላችውም ነፍስ፣ እውነትን መናገር አይገባም፣ ምክንያቱም ያ አያስደስታትምና፡፡ እናንተ የማታምኑ ሆይ፣ እናንተን አላናገርኩምም፣ አላናግርምም፣ እናንተ ዝም በሉ፣ አትሰሙምም፣ እኔ በመናገር ላይ ያለሁት ለሚሰማኝ ነው፡፡ የቃሌ ወይን ካለስደሰታችሁ አትጠጡት፣ ተውት፣ መንጋውን የሚያስደስተው መካን መሬት ነው፡፡
✔❖ ከናንተ ጋር የለፋሁት በመልፋትም ላይ ያለሁት ለምንዳ አይደለም፣ ምሥጋናም ከናንተ አልጠበኩም፣ ደግሞም አለሻውም፡፡ እኔ ከጌታችሁ ስጦታ የመጡትን ነገሮች በማዕድ ጠረጴዛው ላይ አኑሬያለሁ፣ ደስ ካሰኛችሁ ከኛ ጋር ተካፈሉ፣ ካላስደሰታችሁ ተለዩ፡፡ ልቤ (ፈቃዴ) እናንተን በማፍቀር ተወቃሽ አይሆንም፣ ያጣችሁ ስለሆናችሁ ከናንተው ከራሳችሁ ከመጣው ነገር በመካፈል ትጠቀሙ ዘንድ ጠራኋችሁ፡፡
✔❖ ድንግል ወለደች፣ ዓለሙንም ለእራት ግብዣ ጠራች፣ እርሷ የጎደፈች እንደሆነች የሚያስብ ግን እርሱ ከኛ ወገን አይደለም፡፡ የርሷ ልጅ እውነት ነው፣ ድንግልናዋም ሁልጊዜ ይኖራል፣ ይህን መስማት የተሣነው እርሱ ግን ከኛ ጋር አልተጋበዘም፡፡ እርሷ ድንግልም እናትም መሆኗን የምታምኑ ከሆነ በማዕዱ ተቀመጡ፣ መለየትም እምነትም ነፍጓችሁ ከሆነ ለኛ ሥፍራውን ልቀቁልን፡፡ ሌላ ሊያሳምናችሁ የሚችል ገለጻ ፈልጋችሁ ከሆነ፣ ያ እኔን ቅር አየሰኘኝም፣ ለናንተ መድከሜን እቀጥላለሁ፣ በዚያው እኔም ስለምጠቀም፡፡ የማርያም ጉዳይ በከፍታዎች ሁሉ ላይ የተዘረጋ ብርሃን ነው፣ በጨለማ ያለም ቢሰማው ይበራለታል፡፡ የሕይወት ውሃ የፈለቀባት ይህች አዲስ ጉድጉድ፣ ፍፁም ሳትነጥፍ የሚፈሱ ጅረቶችን ለተጠማው ዓለም አመንጭታለች፡፡
የቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ እመቤት ኹላችንንም ትባርከን
የእመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልና በቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ድርሳን ከሚለው መጽሐፌ የተወሰደ
በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
እስቲ እናንተም በተቻላችኊ መጠን እንደ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የአምላክን እናት አወድሷት፡፡